ቀለም ኢትዮጵያ ህገወጥ ስደትን በመከላከል ዙሪያ ትኩረት ያደረገ የሶስት ዓመት ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡

የካቲት 30፣2011 ፕሮጀክቱ 20 ሚሊዮን ብር የሚጠይቅ ሲሆን በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ ክፍሎች የሚተገበር ነው፡፡ ሁሉን አቀፍና በአገራዊ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ያለው ቀለም ኢትዮጵያ አሁን ላይ ይፋ ያደረገው ፕሮጀክት እየተበራከተ የመጣውን የህገወጥ ስደት ከስሩ ለማድረቅ የሚያስችል መሆኑን የቀለም ኢትዮጵያ አመራሮች በፕሮጀክቱ ይፋ ማድረጊያ ስነ ስርዓት ላይ ተናግረዋል፡፡ የካቲት 30፣2011 በደቡብ ወሎ ኮምቦልቻ ከተማ ይፋ በተደረገው በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ከአማራ ክልል ሰሜን ወሎና የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን የተውጣጡ 10 ወረዳዎች ተካፍለዋል፡፡ ከ100 በላይ የባለድርሻ አካላት በተገኙበት የተሳታፊዎች መድረክ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ንቃተ ህሊና በመፍጠር በሁተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ከአረብ አገር በተመለሱና በሌሎች የማህበረሰብ አባላት ላይ የአመለካካት ለውጥ እንዲመጣ መስራት ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ ቀለም ኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የሚቆየውን ይህን ፕሮጀክት ከጀርመኑ ትብብር ቴራ ቴክ ጋር በመተባበር የሚተገብረው መሆኑም ተመልክቷል፡፡ ቀለም ኢትዮጵያ ከተመሰረተበት 1995 ወዲህ ላለፉት 16 ዓመታት በአርብቶአደሮች ትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ፣በጤና፣ በውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን እንዲሁም በአደጋ ጊዜ ምላሽና በማህበረሰብ ኑሮ መሻሻል ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ በየዓመቱ በባህርና በየብስ የሚደረገን ህገወጥ ስደት ከምንጩ ለመከላከል ያለመውን ፕሮጀክት ከጀርመን ትብብር በተገኘ ድጋፍ በቀጣይ አመርቂ ስራዎችን ለመስራት በተመረጡ 10 ወረዳዎች ፕሮጀክቱ በይፋ ጀምሯል፡፡

Written on .

Print