ትምህርት ከክፍል ውስጥ ከሚገኝ እውቀት በላይ ነው። እውቀትን፣ ክህሎትንና በራስ መተማመንን በማዳበር ለተሻለ ሕይወት፣ ለጠንካራ ማህበረሰብና ለዘላቂ ልማት መሠረት ይጥላል።በእውቀት የተገነባ ማህበረሰብ ችግርን ለመጋፈጥ የተሻለ ጥንካሬን ያጎለብታል፡፡ ለዚህም ነው የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሻሻል ብርቱ ጥረቶች የሚደረጉት፡፡
ትምህርትን የማዳረስ ጥረቶች
ዛሬ አለም አቀፍ የማንበብና የመጻፍ ቀን ይከበራል፡፡ ቀኑ ማንበብና መፃፍ ለሰዎች፤ለምንኖርባት ምድርና ለሃገር እድገት ያለውን ወሳኝ ጠቀሜታ በመገንዘብ “Literacy for people, the planet and prosperity” በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የማንበብና የመጻፍ አቅም ስናይ መሻሻል ቢታይም 739 ሚሊዮን ወጣቶችና ጎልማሶች አሁንም ድረስ መሠረታዊ የማንበብና የመጻፍ ክህሎት የላቸውም። በተመሳሳይ የአዋቂዎች የማንበብና የመጻፍ ችሎታ ብንመለከት እ.ኤ.አ. በ1975 ከነበረበት 65% ወደ 88% በላይ አድጓል፣ ነገር ግን እንደ ዩኔስኮ ገለጻ ዋና ዋና ክፍተቶች አሁንም አሉ።ይህ እውነታ ነው እንግዲህ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ጉዳይ የየአገራት ተቀዳሚ ተግባር እንዲሆን ያስገደደው።

ቀለም ኢትዮጵያ ከ23 ዓመታት በላይ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በተለይም በአፋርና በአማራ ክልሎች የትምህርት ተደራሽነት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት በመስጠት የትምህርት ዕድልን ለማስፋፋት እየሠራ ይገኛል።
በአፋር ክልል ብዙሃኑ ነዋሪ አርብቶ አደር እንደመሆኑ መጠን ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ የሚኖር ማህበረሰብ ነው፡፡ተደጋጋሚ እንቅስቃሴና በግጭት ምክንያት መፈናቀል የሚያጋጥመው ማህበረሰብ በመሆኑም ይህ
የኑሮ ዘይቤ መደበኛ ትምህርትን ለማከናወን ተፅእኖ የሚፈጥር ነው። በዚህ መደበኛ ስርአት መማር ላልቻሉ ዜጎች ከኑሮ ዘይቤያቸው ጋር የሚጣጣም የማስተማሪያ ስልትን በመጠቀም ትምህርት ላልደረሳቸው ዜጎች ማዳረስ አንዱ መንገድ ነው፡፡
ለዚህም ሲባል ቀለም ኢትዮጵያ 68 የአንደኛ ደረጃና አማራጭ መሠረታዊ ትምህርት ማዕከላት በማቋቋም ትምህርትን ወደ ማህበረሰቡ
ለማቅረብ ሠርቷል።በተጨማሪም 168 ትምህርት ቤቶችን በማደስና በማሟላት ለመማርና ማስተማር ሂደቱ የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር አስተዋፅዖ አድርጓል።ይህ በተለይ ከትምህርት ገበታ ርቀው ለሚገኙ ልጃገረዶችና ሴቶች የመማር ዕድልን ያስገኘላቸው ወሳኝ ዘዴ ነው።

በተመሳሳይ በአማራ ክልል የሚታየው የትምህርት ቁሳቁስ፣ የላቦራቶሪና የቤተ-መጻሕፍት እጥረት ደግሞ የትምህርት ጥራትን የሚፈትን ነው። ይህን ለመቅረፍ ሲባል ሁሉን አቀፍ የትምህርት ድጋፍና እገዛ ተደርጓል፡፡
ከዚህ ውስጥ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል አጋዥ የሆነውና ቀለም ከአጋሮቹ ጋር በመተባበር እያከናወነ ያለው የEQUIP ፕሮጀክት አንዱ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በአማራ ክልል በኮምቦልቻ ከተማና ቃሉ ወረዳ በሚገኙ 12 ትምህርት ቤቶች በመተግበር ላይ ሲሆን፤የትምህርት ቁሳቁስ ስርጭት፣ የመምህራን ስልጠናና የሥርዓተ-ፆታ ክለባትን በመደገፍ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ረገድ የራሱን አሻራ እያሳረፈ ይገኛል።
ማንበብና መጻፍ ተፅእኖው ሰፊና ከፍተኛ ነው!!

ማንበብና መጻፍ መቻል መረጃን ለማግኘት፣ የተሻለ ውሳኔ ለመወሰን፣ ኑሮን ለማሻሻልና
የኢኮኖሚ ዕድሎችን ለመጠቀም በር ይከፍታል። ስለዚህ በትምህርት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ በትምህርት ቤቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በጠንካራ ቤተሰቦች፣ፈተናን መቋቋም የሚችል ማህበረሰብን መፍጠርና በተሻለ የወደፊት ሕይወት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ነው።
በመሆኑም የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የማንበብና የመጻፍ ቀን “ማንበብና መጻፍ ለሰዎች፣ ለፕላኔቷና ለሁለንተናዊ እድገት” በሚል መሪ ቃል ስናከብር፣ አንድ ነገር እናስታውሳለን፦ይህም “ዛሬ የምናስተምረው ልጅ፣ ነገ ማህበረሰቡን ይገነባል” የሚለው መሪ እሳቤ ነው፡፡
ዛሬ ላይ በትምህርት ዘርፍ የምናፈሰው መዋእለ ንዋይ ነገ ውጤቱ ማህበረሰባዊና አለም አቀአፋዊ መሆኑን መገንዘብ ፋይዳው የላቀ ጠቃሚ እይታ ነው፡፡
ቀለም ኢትዮጵያ ለትህምርት ጥራት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሁለንተናዊ ድጋፍ መስጠቱን ይቀጥላል፡፡
የማንበብና የመጻፍ አቅም ሲያድግ፣ ማህበረሰብ ይበረታል!


